የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ
እኛ ማነን ብሎ መጠየቅ ትልቅነት ነው፡፡ ጥያቄ ከውጭ ወደ ውስጥ ሳይሆን ከውስጥ ወደ ውጭ ሲሆን መልካም፡፡ በእኛው በራሳችን በቤተ ክርስቲያን ልጆች የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ እንዴት ነው ብሎ መጠየቅና ማወቅ ሥልጣኔ ነው፡፡ ምክንያቱም ትናንት የማያውቅና ነገን የማይተነብይ ዛሬ፣ እና አንገት የሌለው ሰው ሁለቱ አንድ ናቸው፡፡ አንገት የሌለው ሰው አዙሮ እንደማያይ ሁሉ ትናንትን የማያውቅ ሰው ዛሬን ማወቅ ስለሚያቅተው ነው፡፡
ዛሬ ብቻ ማለት የራስ ወዳድነት ውጤት ነው፡፡ ትናንት የሌለውን ዛሬን መፍጠር የሚፈልጉ ሰዎች ዛሬ እኛ ዘመርነው፣ ዛሬ እኛ ቀደስነው፣ ዛሬ እኛ ሠራነው እያሉ ትናንት እንዳልነበረና ምንም ከሌለበት የመጣ የተገኘ ይመስል ያለፉት አባቶች ዛሬን እኛን ለማሳየት የከፈሉትን መሥዋዕትነት ይዘነጋል፡፡ ብልህ ትውልድ ግን አስቀድሞ የሀገሩን፣ መሠረቱን፣ የቤተ ክርስቲያኑን ታሪክ ያጠናል፡፡ ታሪክን ጠይቆና አንብቦ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን አስቀድሞ ነቢዩ ሙሴ “አባትህን ጠይቅ ይነግርህማል፣ ሽማግሌዎችን ጠይቅ ይተርኩልህማል፡” በዘዳ.32፣7 የሚለው የነቢዩ ሙሴ የመጨረሻ ምክሩ ነው፡፡
ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን ታሪክ ማወቅ አለብን ስንል ዛሬ እየኖርንባት እየተከተልናት ያለንባትን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንወቅ ማለት ነው፡፡
ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመጽሐፍ ቅዱስ ከ60 ጊዜ በበጎ ተግባር፣ በመልካም ምሳሌ የተጠቀሰች የእግዚአብሔር ሀገር ናት፡፡ ከዚህም የተነሣ በርካታ ቅዱሳን የትውልድ ሀገራቸውን ጥለው ወደዚች ሀገር በመምጣት በትሩፋትና በተጋድሎ የኖሩባት ሀገር ናት፡፡ ይህች ቅድስት ሀገር በመጽሐፍ ቅዱስ ከመጠቀሷ ባሻገር የያዘችው የክርስትና ሃይማኖት ታሪኳ እንዴት እንደሆነ በዚህ ጽሑፍ እናቀርብላችኋለን፡፡
ቤተ ክርስቲያን ማለት በጽርዕ ቋንቋ “አክለሲያ” ማለት ሲሆን ትርጉሙም ለአንድ ዓላማና ሥራ የተመረጡና የተጠሩትን ማኅበር ወይም ጉባኤን ያመለክታል፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ማለት ያመኑ ወገኖች በሰማይም በምድርም የሚገናኙበት፤ በሰማይም በምድርም ያለች ሐዋርያዊትና ክርስቲያኖች ተሰባስበው ጸሎት የሚያደርጉባት፤ ወደ መንግሥተ ሰማያት መውጫ መሰላል፣ የእግዚአብሔር የዐይኑ ማረፊያ፤ የሰማይ ደጅ፤ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታትና የቀደሳት ናት፡፡ (ኤፌ.5:25-26፤ ግ.ሐ.20፣28)
የዚህችን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዴት ነው ስንል የመሠረታት ማነው የሚለውን ጥያቄና የአሠራረቷስ ታሪክ እንዴት ነው ብሎ እንደመጠየቅ ነው፡፡ (አባ ጎርጎርዮስ ቤተ ክርስቲያን በዓለም መድረክ፤1978፤14)
የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በባህሪዋ ዓለም አቀፋዊት፣ ሐዋርያዊት፣ ኩላዊት፣ እና በዓለም ላይ ያለችው ቤተክርስቲያን አንዲት ብትሆንም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዴት ነው የሚለውን ቀጥሎ ማየት እንችላለን፡፡ (1 ጢሞ 3:15፣ ኤፌ 2:22)
የኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ይወስደናል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በዓለመ መላእክት አስቀድማ በሰማይ ያለች ብትሆንም በአካል ገዝፋ በምድር የተገለጥችበት ጊዜ ከሰው ልጆች የአምልኮ ሥፍራ አመሠራረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አስቀድመው ክርስቲያኖች በጋራ በመሰብሰብ የአምልኮ ሥርዓት የሚፈጽሙባት ምኩራብ፣ መልካም የተባለች ሥፍራ፣ ተብላ የምትጠራ ስትሆን፣ ቀጥሎ ቤቴል ከዚያም ቤተ መቅደስ በሚል መጠሪያ ትታወቅ ነበር፡፡
ከሐዲስ ኪዳን ሥርዓት በኋላ ፣ ቤተ መቅደስ የሚለው ስም ሳይጠፋ በሰፊው ቤተ ክርስቲያን ወደሚል መጠሪያ ተሸጋግራለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ትርጉም አለው፡፡ የመጀመሪያው የክርስቲያኖች ኅብረት፣ ሁለተኛ የሰው ልጅ በራሱ ሦስተኛው የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚገኝበት ለእግዚብሔር የተለየ ቅዱስ ሥፍራ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተብላ እስከ ዛሬ ትታወቃለች፡፡ የጸጋው ግምጃ ቤት፣ የምሕረቱ ማኅደር ናት፡፡ ከእሷውጭ መዳን የለምና፡፡ (ራዕ.5፣9-12)
በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በተጠቀሰው መሠረት ያለች ስትሆን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዓለም ላይ በበዓለ ጰራቅሊጦስ በማርቆስ እናት ቤት እንደተመሠረተች መጽሐፍ ቅዱስ ያስረተዳናል፡፡ (ግ.ሐ.12፣12) ከዚህም በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያት፣ ሐዋርያነ አበው፣ ቅዱሳን ሊቃውንት አባቶቻችን ለወንጌል በየተሰማሩበት ሁሉ ክርስቲያኖችን እያስተማሩ በመከራም በደስታም ውስጥ ሆነው ቤተ ክርስቲያንን እየሠሩ እስከ ዛሬ አድርሰውልናል፡፡
በቅድስት ሀገር ኢትዮጵያም የሐዲስ ኪዳን ትምህርት የሰበኩን እነ ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ በ34 ዓ.ም. ባስተማሩት መሠረት በሐዲስ ኪዳን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዳግመኛ ሠርተዋታል፡፡ (ግ.ሐ.8.26-40) በኋላም በነ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን በ3ኛው መ.ክ.ዘ ዓ.ም አካባቢ በስፋት በመላው ኢትዮጵያ መሠራት ጀምራለች፡፡ ቀትሎ ጠዘኙ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ ምጣት ጉልህ ድርሻ እንደነበረው ይገልጻል፡፡ (ግርማ ባቱ፤180)
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባም ይሁን የዘጠኙ ቅዱሳን እንዲሁም የአባ ፍሬምናጦስ አስተዋጽዖ የእነሱ ብቻ ሳይሆን የሕዝቡም ተሳትፎ ነበረበት፡፡ ምክንያቱም አስቀድመው ትንቢተ ነቢያትን የሚያምኑና የሚጠባበቁ መሆናቸውን ጌታችን በተወለደ ጊዜ ሊሰግዱ ከሔዱ ነገሥታት መካከል ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ባዜን 1 ምስክር ነው፡፡ (ማቴ.2፣1) የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻ ያመጡለታል፡፡ (መዝ.72፣9-11) ተብሎ የተጠቀሰው ያን ጊዜ ጌታ በተወለደ ሰዓት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ክርስትናን ለመቀበል አልዘገየችም፤ አስቀድማም ታውቀው ስለነበር፡፡ የሌሎችን ዓለማት የክርስትና ታሪክ ስናጠና ሐዋርያትን አሰቃይተው፣ ገርፈው፣ ሰቅለው፣ ቆዳቸውን ገፈው፣ በመሬት ጎትተው ከገደሉ በኋላ ያመኑ ናቸው፡፡ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ደግሞ በፍቅር በአክብሮት ተቀብላ የእግዚአብሔር መልእክተኞች ብላ የተቀበለችው አስቀድማ የተዘጋጀት መሆኗን ለማጠየቅ ነው፡፡
ከጌታችን ልደት በኋላ በዘመነ ሄሮድስ ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ቅዱስ ዮሴፍና ሰሎሜ በጉዟቸው ኢትዮጵያውያን ተንከባክበው የተቀበሏቸው ያ ቅዱስ ጉዞ (ኢሳ.19፣1) ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መመሥረት ሌላቸው አስተዋጽኦ እንደሆነ በጉልህ መታሰብ የሚገባው ነው፡፡ ዛሬም ድረስ በጣና ገዳማት፣ አክሱም ጽዮን ታቦተ ጽዮን ያለችባት በመሆንዋ፣ በዋልድባና በሌሎችም ቅዱሳን ሥፍራዎች ዞረው በመባረክ ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ምክንያት እንደሆኑ እንድንረዳ ያርገናል፡፡
ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ሊሰግድ በየዓመቱ ወደ ኢየሩሳሌም ይሔድ እንደነበረ በተጠቀሰው መሠረት ሌሎች ኢትዮጵያውያንም በየዓመቱ የፋሲካን በዓል ለማክብርና ለመሳለም ወደ ኢየሩሳሌም ይሔዱ እንደነበር መንፈስ ቅዱስ በወረደ ጊዜ በዚያ እንደነበሩ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጠቅሶ (ግርማ ባቱ፤ 201) ያስረዳል፡፡ የወንጌላዊው ማቴዎስ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ወንጌልን የመስበኩ ጉዳይ በሰፊው የሚተክላት ኢትዮጵያ እምነቷ በአባቶቻችን ስብከት ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡